About US

የዉሃ ዋና ታሪክ የኢትዮጵያ

መቼና የት እንደተጀመረ ባይታወቅም ቀደም ብሎ የውሃ ዋና እንቅስቃሴዎች በኢትየጵያ እንደነበር ይታመናል፡፡ በሀገራችን የዉሃ ዋና ዓይነት ስሞች እንደየአካባቢው ይለያይ ነበር፡፡ ከእነዚህ እንቅስቃሴች መካከል የጎን ዋና፤ የቁም ዋና እና ጉስጉስ የሚባሉት በጣም የሚታወቁ ነበሩ፡፡ እነኚህም የውሃ ዋና አይነቶች በሀገር ቤቱ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ የሚዘወትሩ ሆነው ማህበረሰቡም ወንዞችን ለመሸገርም ሆነ እንስሳትን ለማሻገር ወይም ለጦርነት ዝግጅት ይጠቀሙበት እንደነበር ታሪክ ይነጋራል፡፡ ዘመናዊ የውሃ ዋና ስፖርት በኢትዮጵያ ኮሞላ ጎደል ተጀመረ ለማለት የሚቻለው ከ50 ዓመታታ በፊት ሲካሄዱ በነበሩት የጦር ኃይሎች ዓመታዊ የስፖርት ውድድሮች ወቅት ነው፡፡ ይህውም የውሃ ዋና ውድድሮችን በተወሰነ ሰዓት ማካሄድ የተጀመረው በ1950 እና 1951 ዓ.ም. ቢሾፍቱ በሚገኘው ሆራ ሐይቅና በአየር ኃይል የመዋኛ ስፍራ በተደረጉት የጦር ኃይሎች የውሃ ዋና ስፖርት ውድድሮች እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በወቅቱ ከነበረው የውሃ ዋና ታሪክ ለመረዳት እንደሚቻለው በተለይም የቀድሞ የባህር ሀይል ዓመታዊ የካዴቶች ምረቃ በዓል ከተለያዩ ሀገሮች ከሚመጡ ስፖርተኞች ጋር በሚደረገው የውሃ ዋና ውድድር ዘመናዊ ቴክኒኮችን ለመቅሰም እንደተቻለ ይነገራል፡፡

ከላይ በተጠቀሰው በአብዛኛው በወታዳሩ ክፍል ተወዶ የቆየው የውሃ ዋና ስፖርት ከጊዜ በኋላ በተለይም በግዮን ሆቴል የመዋኛ ስፍራና በሌሎችም ቦታዎች የተወሰኑ ት/ቤቶች የስፖርት ክለቦችና ሌላው ህብረተሰብ በስፋት እንዲሳተፍበት ለማድረግ በመቻሉ ስፖርቱን ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር አጋጣሚዎች ተፈጥረዋል፡፡ ይህውም በተለይ 1970 ዓ.ም. በተወሰኑ የስፖርቱ አፍቃሪ ግለሰቦች አማከይነት የዋና ስፖርትን በሀገራችን ለማስተዋወቅና በዘመናዊ መልክ ለማስፋፋት የተሻለ እንቅስቃሴ በመደረጉ በአዲስ አበባ በግዮን ሆቴል የመዋኛ ስፍራ የውሃ ዋናን በግላቸው ሊያዘወትሩ የነበሩ ግለሰቦችንና ወጣት ዋናተኞችን በማሰባሰብና በማበረታታት ለመጀመሪያ ጊዜ የፊንፊኔ የውሃ ዋና ክለብ ሊቋቋም ችሏል፡፡

የስፖርቱ አፍቃሪዎችም በዚሁ አጋጣሚ ቁጥራቸው እየጨመረ በመምጣቱ ስፖርተኞችን የሚያቅፉ ክለቦች ለማደራጀት ህጋዊ አቋም ያለዉ የውሃ ዋና ስፖርት መምሪያ በአካል ማሰልጠኛና ስፖርት ኮሚሽን ታውቆ በመቋቋሙ መደበኛ የውድድር እንቅስቃሴዎች እንደተጀመሩ ይነገራል፡፡

የኢትዮጵያ ውሃ ዋና ፌዴሬሽን አመሠራረት የኢትዮጵያ ዉሃ ዋና መምሪያ ከ1970 ዓ.ም. ጀምሮ በመምሪያ ደረጃ ተቋቁሞ ክለቦችን ለማደራጀትና ውድድሮችን በየደረጃው ለማካሄድ ይንቀሳቀስ የነበረ ሲሆን የውሃ ዋና ስፖርት መምሪያ ተፈላጊ መስፈርቶችን እንዲያሟላ ከታደረገ በኋላ በ1971 ዓ.ም በመጋቢት ወር ላይ የኢትዮጵያ ውሃ ዋና ፌዴሬሽን ተብሎ ተመሠረተ፡፡ ፌዴሬሽኑ ከተመሠረተ በኋላ ውስጣዊ አቋሙን በማጠናከር የተወሰኑ ስልጠናዎችንና ውድድሮችን ሲያካሄድ ቆይቶ በ1975 ዓ.ም. የዓለም አቀፍ ውሃ ዋና አማተር ፌዴሬሽን ማህበር (FINA) እና የአፍሪካ ውሃ ዋና አማተር ኮንፌዴሬሽን ማህበር (CANA) አባል በመሆን በወቅቱ ስፖርቱ በህብረተሰቡ ዘንድ እንዲዘወተር ለማድረግ ከፍተኛ እንቅስቃሴዎችን ተደርጎዋል፡፡
ፌዴሬሽኑ ስፖርቱ ሊስፋፋና በህዝብም ዘንድ ተወዳጅነት ሊያገኝ የሚችለው የውሃ ዋና ስፖርት አፍቀሪዎችና ተወዳደሪዎች በተደራጀው ተቋማት ታቅፈው ሊንቀሳቀሱ መሆኑን በመረዳት ከ20 የማያንሱ ክለቦችን መዝግቦ በአዲስ አበባ ግዮን መዋኛ ስፍራና፣ በአምቦ፣ በሶደሬ፣ በቢሾፍቱ /ሆራ/፣ በወሊሶና በሌሎች በተወሰነ ደረጃ የመዋኛ ስፍራዎች ባላቸው ከተሞች ማለትም ባህርዳር፣ አዋሳና ድሬዳዋ በየደረጃው የዉሃ ዋና ውድድሮችንና መሠረታዊ ስልጠናዎችን ያካሄድ እንደነበር ይታወቃል፡፡

ከመደበኛ የዉሃ ዋና ውድድሮች በተጨማሪ የውሃ ላይ ኳስ ጨዋታ (water polo) እና የመጥለቅ (Diving) ውድደሮችን በክለቦችና በአገር አቀፍ ደረጃ ያወዳድር እንደነበር ይታወቃል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከ1975 ዓ.ም. ጀምሮ በርካታ ክለቦችን በማሣተፍ ውድድሮችን በተሻለ ዝግጅት ሊያካሄድ የነበረው የአዲስ አበባ ስፖርት ምክር ቤት የውሃ ዋና ኮሚቴ በወቅቱ በአርአያነት ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡ ነገር ግን ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ለፌዴሬሽኑ እንቅስቃሴ አዝጋሚ ሆኖ መገኘት የሚጠቀሱት ምክንያቶች የተለያዩ ቢሆንም የውሃ ዋና ስፖርቱን በሀገራችን ለማስፋፋትና ለማፋጠን የማዘውተሪያ ስፍራዎችን በየቦታው ማመቻቸት፣ ተገቢ የሆኑ ስልጠናዎችን በየደረጃው የመስጠትና ክለቦችን በየደረጃው የማደራጀቱ ተግባር ወሳኝነት እንደሚኖረው ግልፅ
ነው፡፡ ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ውሃ ዋና ፌዴሬሽን በመባል ይጠራ የነበረዉ በአሁኑ ጊዜ ስያሜዉ ተቀይሮ የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ተብሏል፡፡


• በመላ ሀገሪቱ የውሃ ስፖርቶች ልማት እና ማስፋፋት ላይ መስራት;
• ሁሉንም የሀገሪቱ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ሁሉን አቀፍ የውሃ ስፖርቶች ዝግጅቶችን ማደራጀትና ማስተዳደር፣
• ለስፖርት ባለሙያዎች እና ለወጣቶች የስፖርት ማሰልጠኛ መርሃ ግብር የሀገር ውስጥ እና አለም አቀፍ ስልጠናዎችን ማደራጀት እና የዘርፉን ሙያዊ ብቃት ማጠናከር;
• ስፖርተኞችን ከዶፒንግ እና ሌሎች በተፈጥሮ ችሎታዎች ላይ ተጽእኖ ሊያሳድሩ ከሚችሉ ነገሮችን ለመከላከል;
• ሀገርን በመወከል በአህጉራዊ እና አለም አቀፍ ውድድሮች ላይ መሳተፍ;
• በስፖርት ቤተሰብ መካከል ሀገራዊ ወዳጅነትን፣ እህትማማችነትን እና ትስስርን በማጠናከር ለስፖርታዊ ጨዋነት ከፍ ያለ ክብር በመስጠት የስፖርቱን እሴቶች ማስጠበቅ እና መጠበቅ፤
• አለመግባባቶችን ለመፍታት በክልላዊ እና በክለብ ውድድር የሚነሱ ጉዳዮችን በኢትዮጵያ የውሃ ስፖርቶች ፌደሬሽን እና የአለም የውሃ ስፖርቶች ህግ መሰረት መፍታት፤